የትምባሆ ምርቶች የጤና፣የማህበራዊ፣የኢኮኖሚ እና አካባቢያዊ ችግር የሚያስከትሉ በመሆናቸው፤ ትምባሆን መጠቀም እንደ ካንሰር፣ የመተንፈሻ አካል ህመም፣ የልብ እና የደም ስር የመሳሰሉትን በሽታዎች፣ የአካል ጉዳትን እንዲሁም ሞትን እንደሚያስከትል በሳይንስ የተረጋገጠ በመሆኑ፤ ለትምባሆ ጢስ መጋለጥ ትምባሆ በማያጨሱ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር፤ ሞት እና የአካል ጉዳት ስለሚያስከትል እና ይህንኑ መቆጣጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ በሀገሪቱ ትምባሆን የሚጠቀሙ ወጣቶችና ጎልማሶች ቁጥር እንዳይጨምር፤ የትምባሆ ምርትን ማስተዋወቅ፣ ፕሮሞት እና ስፖንስር ማድርግ ትምባሆ የመጠቀም ፍላጎትን እንዲጨምር የሚያደርግ በመሆኑ እና ይህንን የትምባሆ ሽያጭ መንገድ መቆጣጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኝቱ፤ በአለም የጤና ድርጅት የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን መሰረት መንግስት የትምባሆ ምርት መጠቀም እና የትምባሆ ጭስ ተጋላጭነትን ከመከላከል እና ለመቀነስ ግዴታ በተጨማሪ የኒኮቲን ንጥረነገር ሱሰኝነት እና ጥገኝነት የመከላከል እና የመቀነስ ሀላፊነት ስላለበት፤ የኒኮቲን ንጥረ ነገር ያለውም ይሁን የሌለው የኤሌክትሮኒክ ኒኮቲን መስጫ መሳሪያ (Electronic Nicotine Delivery System) መጠቀም ለትምባሆ ተጠቃሚዎች ተቀጣጣይ ትምባሆን (combustible tobacco) ከመጠቀም በአንፃራዊ መንገድ ያነሰ ጉዳት እንዳለው ቢገለጽም በአሁኑ ሰአት በሀገራችን የትምባሆ ተጠቃሚነት ስርጭት ዝቅተኛ ስለሆነ እና የህብረተሰብ ጤና በተለይ የማያጨሱ ሰዎች፣ ህጻናትን፣ ነፍሰጡር እናቶች እና ሌሎች ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍል በአግባቡ ለመጠበቅ ሲባል እና በመተግበር ላይ ያሉ የትምባሆ ቁጥጥር ስራዎችን ዉጤታማ በሆነ መልኩ ለማስፈጸም እንዲቻል ይህንን ምርት በህግ መከልከል አሳማኝ ሆኖ በመገኘቱ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን የትምባሆን ቁጥጥር በተመለከተ በአለም የጤና ድርጅት የወጣውን የትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን ማጽደቂያ አዋጅ ቁጥር 822/2006 ለማስፈጸም አስፈላጊ እርምጃዎችን እንዲወስድ ስልጣን የሰጠው በመሆኑ፤ በትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽኑ ውስጥ ካሉ የትምባሆ ቁጥጥር ስራዎች ውስጥ የተወሰኑ ስራዎችን ለክልል መንግስት መስጠቱ ኮንቬንሽኑን በአግባቡና ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ለማስፈፀም የሚረዳ እና አስፈላጊ እርምጃ ሆኖ በመገኘቱ፤ በትምባሆ ቁጥጥር ኮንቬንሽን ማጽደቂያ አዋጅ ቁጥር 822/2006 አንቀጽ (4)፣ በአዋጅ ቁጥር 661/2002 አንቀጽ 55(3) እና በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 299/2006 አንቀጽ 98 መሰረት የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን ይህን የትምባሆ ቁጥጥር መመሪያ አውጥቷል፡፡